ይህ ሰማይ ለብዙዎች በተለይም ለቱሪስቶች ተራ ሰማይ አይደለም ፡፡ ከሰማዩ በታች ያለው ዳመና የደመቀ ነጭ ነው ፡፡ ከዳመናው በሚምዘገዘግ የፋልኮ ፍጥነት መሬት ቢደርሱ የሚያገኙት ከነጭ ቀለም አፍቃሪዎቹ ሙርሲዎች ጋር ይሆናል ፡፡

ልብ ላለ ተመልካች ነጩ ዳመና እና በነጭ የተዥጎረጎረው የሙርሲዎች ገላ የሚያገናኛቸው መስተጋብር አይጠፋም ፡፡ ዳመናው ከሰራቸው የተለያዩ ቅርጾች መካከል ነጫጭ የላም ግልገሎችን ለአፍታም ቢሆን መመልከት ይቻላል ፡፡ የሙርሲዎች ነጫጭ ገላ ላይ ደግሞ የወተት መጠጫ ቅልና ከብቶችን ማገጃ አርጩሜ  ፡፡

ከሙርሲ ሰማይ ስር የነገሱት እጅ ለእጅ የተጨባበጡ ዓይነ ግቡ ተራራዎች ብቻ አይደሉም ፡፡ ሀገራችን ውስጥ ከቀረው የደን ሽፋን አብዛኛውን የሚወክለውን ልዩ ልዩ ዕጽዋት ብቻ አይደለም … ከተሜነት በፈጠረው ጣጣ ያልቆሸሸውን ሽንጠ ረጅም የኦሞ ወንዝ ብቻ አይደለም … ማጎና ብሄራዊ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙትን ትናንሽና ትላልቅ የዱር እንስሳትን ብቻ አይደለም … አዎ ! ከሙርሲ ሰማይ ስር ገዝፈውና ደምቀው የሚታዩት ልዩ ተክለ ሰውነት ያላቸውን ሙርሲዎችን ጭምር ነው ፡፡

ምድረ ፈረንጅ በዚህ ሰማይ ስር ለማዋልና ማደር እየበዛ የሚገኘው ያለ ምክንያት አይደለም ፡፡ ፈረንጅ ጅብደኛ ተግባራትን ለመፈጸም ብቻ ሳይሆን የተጨበጨበላቸውን ጅብደኛ ጉዳዮችንም አድኖ ለመመልከት ወደ ኃላ አለማለቱ ነው ፡፡ በሀገራችን ብቻ የሚገኙ አጥቢ እንስሳትን ማለትም ዋሊያ ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ ፣ የሚኒሊክ ድኩላ ፣ ቀይ ቀበሮ ፣ የስዋይን ቆርኬና የደጋ አጋዘን በብዛት የሚመለከተው በሌላው ዓለም የማይገኙ ልዩ ፍጥረታት ስለሆኑ ነው ፡፡ እኛ ስያሜ አልሰጠናቸው ይሆናል እንጂ ፈረንጆች ልዩ ባህል እና ትውፊት እያሳዩ የሚገኙ ሰዎችንም ‹‹ Endemic Race ›› እያሉ የሚጠሯቸው ይመስለኛል ፡፡

‹‹ Endemic ›› ከሆኑ የሃገራችን ጎሳዎች አንደኛው ደግሞ ሙርሲ ነው ፡፡ ለዚህ አባባል ደግሞ ቢያንስ ሁለት መገለጫዎች ይኖረኛል ፡፡ ከንፈሩን ተልትሎ / በአሁኑ ወቅት / ገል የሚያስቀምጥና ራቁቱን በዱላ የሚከታከት ብሄረሰብ በየትኛውም የዓለም ጫፍ አይገኝም ፡፡ ይህ ተግባር እንደ ጅልነትም ሆነ እንደ ጀግንነት ቢቆጠር ሲታይ ግን ያዝናናል ፤ ያስገርማል ፡፡ ምናልባትም ለተጨማሪ የምርምር ስራ መንገድ ይከፍታል ፡፡

በቅርቡ ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን ለስራ ስንቀሳቀስ ያየኃቸው ሙርሲዎች በእኔ ጭንቅላት እንኳ የትየለሌ ጥያቄዎች እንዲፈጠር አድርገዋል ፡፡ እውነታውን ፣ ትዝብቴንና ጥያቄዎችን ወደ ኃላ በተዋሃደ መልኩ አቀርበዋለሁ ፡፡ በቅድሚያ ግን ከአምላካቸው ወቀሳ ወይም ጉሸማ ሳይደርስብን ማንነታቸውን በስሱ ማስተዋወቅ ይኖርብናል ፡፡

ሙርሲዎችን በግርድፉ

 በነገራችን ላይ እምነታቸው Animism ነው ፡፡ ይህ እምነት ነፍስ የሚኖረው በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በድንጋይ ፣ እንስሳና ዕጽዋትም ጭምር ነው ብሎ ያምናል ፡፡ ቅዱስ መንፈስም በተራራ ፣ ወንዞች ፣ መብረቅና ብርሃን ወስጥ ይኖራል ይላሉ ፡፡ ይህ ፍልስፍናና ሙርሲዎች ያሉበት አካባቢ የተገጣጠመ ይመስላል ፡፡ ሁሌም ተራራ ፣ ወንዝ ፣ ደንና እንስሳት መሃል ይገኛሉ ፡፡ ለግዜው አፍን ሞልቶ መናገር የማይቻለው ስለ መብረቁ ነው ፡፡ የሚያስፈራውም ይህ ‹‹ መብረቅ ›› በፈለጉት ግዜ የሚታዘዝላቸው ከሆነ ነው ፡፡

‹‹ ምታ ብዬሃለሁ ጌታዬ ያን አበሻ ! የነገር ወጌሻ !! ››

‹‹ አሎሎህን ወርውር ! በነጫጭባው ስር !! ››

ባሉ ቁጥር ከተፍ ካለ ነገር ተበላሸ ፡፡ ደግነቱ ለእከካም ሰው ጥፍር እንደሚታዘዝለት አስቀድሞ መጻፉ ወይም መነገሩ ነው ፡፡

ሙርሲ ወይም ሙርዙ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ሲሆን የኦሞ ወንዝና የማጎ ብሄራዊ ፓርክ ከቧቸዋል ፡፡ ለደቡብ ሱዳንም ቅርበት አላቸው ፡፡ በ2007 በተደረገ ቆጠራ ብዛታቸው 8 ሺህ አካባቢ ነበር ፡፡ አሪ ፣ ባና ፣ ቦዲ ፣ ካራ ፣ ክዌጉ ፣ ሚንና  ኛንጋቶም የተባሉ ብሄረሰቦች ይጎራበቷቸዋል ፡፡ ከኒሎ ሳሃራ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ የሚመደቡ ሲሆን ሙርሲ የተሰኘ የራሳቸው መግባቢያ አላቸው ፡፡

የሙርሲ ልጃገረድ እድሜዋ 15 እና 16 ሲደርስ የታችኛው ከንፈሯን በእናቷ ወይም በጎረቤቶቿ ተተልትላ ገል እንድታንጠለጥል ይደረጋል ፡፡ የሙርሲ ወንድም ፊቱንና ሰውነቱን ነጭ ቀለም በመቀባት ይታወቃል ፡፡ ህይወታቸው በዋናነት የተመሰረተው በከብት እርባታ ላይ ሲሆን እርሻ በተከታይ የሚከናወን ተግባር ነው ፡፡ የከብት ደም ፣ ወተት ፣ ቅጠላ ቅጠልና የማሽላ ገንፎ ዋነኛ ምግቦቻቸው ናቸው ፡፡ የከብት ርባታ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ለሀብት መለኪያነት ብቻ ሳይሆን ከጋብቻ ባህል ጋር ቀጥተኛ ትስስር ስላለው ነው ፡፡ በአማካይ አንድ ወንድ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ከብቶች እንደሚኖሩት ይገመታል ፡፡ እነዚህ ከብቶች ለልዩ በዓል ካልሆነ በስተቀር አይታረዱም ፡፡ ሙርሲዎች ከስጋ ይልቅ ደምና ወተትን መጠቀም ይመርጣሉ ፡፡ ለከብቶቻቸውም ይዘፋፍናሉ ፡፡ ያገባች ሴት ሁለት የፍየል ቆዳ ከፊትና ከኃላ ትለብሳለች ፡፡ ልጃገረድ ከሆነች ግን አንድ ወጥ የፍየል ቆዳ ነው የምታደርገው ፡፡

ሙርሲዎችን በግርድፉ ከተዋወቅን ተናጥላዊ ጉዳዮቻችንን በመምዘዝ ዝርዝር ምልከታችንን ለማስከተል ያመቸናል ፡፡ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል በፓርክ፣ በተፈጥሮ ሃብትና በልዩ ልዩ ብሄረሰቦች መኖሪያነቱ የበለጸገ ነው ፡፡ እነዚህ ገጽታዎች ቱሪስቶችን ለመሳብ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ ፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ደቡብ የሚያመራው ጎብኚ ቀልቡን እየሰጠ ያለው ሠብዓዊ ጉዳዮች ላይ ይመስላል ፡፡ ዘመናዊውና የበለጸገው ዓለም ሲያራምደው ከቆየው ማህበራዊና ባህላዊ ፍልስፍና አንጻር የሚቃረኑ እውነቶች መኖራቸውን ከሰማ እውነቶቹን ማየት ብቻ ሳይሆን እግረ መንገዱን የእውቀቱን ጥግ ለመፈተሸ ይጠቀምበታል ፡፡

ምሳሌ ፤

‹ ከንፈርን መተልተል ከውበት ጋር እንዴት ይዛመዳል ? ከንፈር በጥሶና ጥርስን ነቅሎ መናገርና መመገብ እንዴት ይቻላል ? ቀለምን እንደ ልብስ በመጠቀም ራቁቱን የሚኖር ህዝብ የኑሮ ዘይቤ ከ 21 ኛው መቶ ክ/ዘመን አስተሳሰብ ጋር እንዴት ይጣጣማል ? በአውሮፓ የራቁት ዘመን እየመጣ ያለው ፋሽን በሚባለው ወረርሽኝ አማካኝነት ነው ፤ በኢትዮጽያ ያለው ራቁትነት በጋርዮሽ ስርዓተ ማህበር የተተከለው ነው ፡፡ በርካታ ዕድገቶች ሲመጡ የዓለም ህዝቦች በንፋሱ አማካኝነት የቅርጽና ይዘት ለውጦችን ያመጣሉ ፡፡ ይህ ንፋስ እነ ሙርሲን ለመለወጥ ያልቻለው ለምንድነው ? ›

ጎብኚው እነዚህንና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ያነሳል ፡፡ ምላሻቸውን በቀላሉ ካገኘ እሰየው ነው ፡፡ ይረካል ፡፡ ጥያቄዋቹ ግን ጥልቅ ጥናትና ምርምር ስለሚያስፈልጋቸው ብዙዎቹ ቱሪስቶች ለሚያዩት እንጂ ለምላሹ ግድ የላቸውም ፡፡ ምክንያቱም ምላሾቹ በቂ ያልሆኑ ፣ በጥናት ያልተደገፉ ፣ በአፈ ታሪክና በግምት ላይ የተመሰረቱ ሊሆኑ ስለሚችሉ የሚሰማውን የመጨረሻ አድርጎ አይወስድም ፡፡ ባይሆን ለራሱና ለሀገሩ ሊቃውንት የቤት ስራ ሰንቆ ሊሄድ ይችላል ፡፡ በአንድ በኩል የግሎባላይዜሽን አደጋ በሌላ በኩል የተፈጥሮን ስነ ምህዳር አጠባበቅ በማነጻጸር በአዲስ አተያይ ውስጥ ህሊናው እንዲቀዝፍ ዕድል ይፈጥራል ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር መጽሀፍ ለመጻፍ ፣ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ማቋረጫ ለማይኖረው የሚዲያ ክርክር አሪፍ ግብዓት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ፡፡

ያላለቀ ውበት

የሙርሲ ብሄረሰብ ልዩ ከሆነበት አንደኛው ገጽታ የሴቶች ከንፈር ጉዳይ ነው ፡፡ አብዛኛው ሴቶች ከንፈራቸውን ሲተለተሉ የታችኛዎቹን ጥርሶችም ያስወግዳሉ ፡፡ ምክንያቱም ጥርሱ ካለ ገሉን በአግባቡ ለማስቀመጥ ስለማይቻል ፡፡ አንድ ሴት ገል በሚያንጠለጥለው ከንፈር ትወደስ እንጂ ጥርሷን በመንቀሏ የምታገኘው ሞራላዊ ጥቅም የለም ፡፡ ጥርስ ለከንፈር ውበት ሲል ራሱን መስዋእት ያደረገ አካል በመሆኑ ሊታዘንለት በተገባ ነበር ፡፡

በታሪክ ሱያ የተባሉ የብራዚል ወንዶች ፣ ሳራ የተባሉ የቻድ ሴቶች ፣ ማኮንዴ የተባሉ የሞዛምቢክ ሴቶች ከንፈራቸውን ይተለተሉ ነበር ፡፡ ይህ ድርጊት ግን ዛሬ ቆሟል ፡፡ ያልቆመው በኢትዮጽያ ብቻ ነው ፡፡ በርግጥ በሀገራችን ድርጊቱ ከመጥፎ ባህላዊ ድርጊቶች ጎራ የተቀላቀለ ቢሆንም መጥፎነቱ ተጨብጭቦለት ፍጻሜ ማግኘት አልቻለም ፡፡ ለምን ? የሚለው ጥያቄ ብዙ ምላሾችን የሚያስከትል ነው ፡፡

ሙርሲዎች እኛ መጥፎ ያልነውን ድርጊት ገልብጠው አይደለም አዙረው ለመመልከት ፍቃደኛ አይሆኑም ፡፡ ማነው ዛሬ በጣም ከረፈደ ተነስቶ ሺህ ዘመናት ያሳለፈውን ‹ አውነት › - ‹ እውሸት › መሆኑ የተገለጠለት ? የዛሬ ወጣቶች በትምህርትና ባህል ፍትጊያ መሃል የሆነ አዲስ ሀሳብ ፈንጥቆ ሊታያቸው ቢችልም ማህበረሰቡን የሚመራው አዛውንት ክፍል አንድም ለቆየው ባህሉ በሌላ በኩል እያገኘ ካለው ጥቅም አኳያ ከንፈር ትልተላን የተመለከተ አዲስ አንቀጽ ለመጨመር ከልቡ ፍቃደኛ አይሆንም ፡፡ የቱሪስቶች ልዩ ነገር የመመልከት ፍላጎት ፣ የአስጎብኚ ድርጅቶች ዓመታዊ የገቢ እቅድ ፣ የመንግስት አገም ጠቀም አሰራር ሁሉ ሁኔታውን ለመቀየር የሚያስችሉ አይደሉም ፡፡

የከንፈር ትልትላው ታሪካዊ መነሻንም መፈተሸ ወሪያችንን ሊያዳብር ይችላል ፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚገልጹት የሙርሲ ሴቶች ከንፈር ላይ የሚቀመጠው ገል ቀደም ባለው ግዜ ጥቁሮች ከመታደንና ለባሪያ ንግድነት ከማገልገል ዉጪ እንዲሆኑ አድርጓል ፡፡ በዚህ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት አካልን መተልተል የቁንጅና ሳይሆን የፉንጋነት ምልክት ነበር ማለት ነው - የማምለጫ ፋይዳ ፡፡ / እንዲህ ከሆነ ኢትዮጽያ ፉንጋ ለማሳየት ፈረንጆችን የምታሰልፍ ብቸኛ ሀገር ልትሆን አይደል ?! ይህ ሀሳብ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ጥሩ ስላልሆነ ከቅንፍ እንዳይወጣ ተደርጓል / የትልተላው መነሻ ፍንገላን ለመከላከል ከሆነ መቼም ዛሬ የባሪያ ንግድ በህግ መቆሙ ይታወቃል ፡፡ ምናልባት ያላወቅነውና የስነ ልቦና ቅኝት የሚፈልገው ሙርሲዎች ዛሬም የባሪያ ንግድ አለ ብለው ሳያስቡ አይቀርም የሚለው ጉዳይ ነው ፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ የሙርሲ ሴቶች ከንፈርና ገል እንደ አክሱም ሃውልቶችና ላሊበላ ውቅሮች የገዘፈ ስም አግኝተዋል ፡፡ በመሆኑም የሙርሲዎች ‹ መብረቅ › የተለየ ትዕዛዝ ካላስተላለፈ በስተቀር በብዙ መቶ ሺዎች መጎብኘታቸውን ይቀጥላሉ ፡፡

ይህ እስከ 16 ሴ.ሜ ሰፍቶ ገል የሚሸከመው ከንፈር በግርማ ሞገሱ ትንሽ ትልቁን እንዳስደመመ አይቀጥልም ፡፡ ገሉ ከመሃሉ ሲለየው ቀልቡ እንደተገፈፈ ውሻ ሁለመናው ጥምልምል ብሎ የሚደበቅበት ቦታ የሚፈልግ ይመስላል ፡፡ ቋንጣ የመሰለው ከንፈር ይሄኔ / በእኔ አይን / ያስጠላል ፡፡ ካልተኙ በስተቀር እንደ ፔንዱለም ወዲህ ወዲያ የሚጨፍር በመሆኑ ሀሳብ እንዳይሰበሰብ ያደርጋል ፡፡

እንደው ለመሆኑ የሙርሲ ወንድ ይህን ዝልዝል ከንፈር እንዴት ነው Adress የሚያደርገው ? በስሱ ይስመዋል ወይስ በከፊል እያስገባ ያስወጣዋል ? ነው የታችኛው ተጠሪነቱ ለሸክላ የላይኛው ለአባወራው ይሆን ? የአክሱም ሃውልት ለጉራጌው ምኑ ነው  ያለው ታዋቂ ሰው ማን ነበር ? ከዓለም ለተለየው ሙርሲ  ‹ የፈነዳ ከንፈር … እንቡጥ ከንፈር … ምራቅ የሚያበዛ ከንፈር … › የተሰኙ አጓጊ ገለጻዎች ለሙርሲው ምኑ ነው ?

ከንፈራቸውን ለመተልተል ፣ የሚያጠልቁትን ገል ውበት በተላበሰ መልኩ ለመስራት የማይሰንፉት የሙርሲ ሴቶች ከንፈራቸው ደምቆ ውሎ ደምቆ እንዲያድር የሆነ መላ አለመፍጠራቸው ግን ይገርማል ፡፡ ከሰሩ ላይቀር አገጫቸውን ሰንጠቅ አድርገው የተንዘለዘለውን ስጋ ተጠቅልሎ እንዲደበቅ ቢያደርጉ ምን ነበረበት ? ካንጋሮ እንኳን ሆዷ ላይ ባላት ኪስ ቢጤ ነገር ነው ልጆቿን ከታ የምትሮጠው ፡፡ የአገጩ ባይቻል እንኳን ይህን የተንጠለጠለ ስጋ/ ስራውን ከጨረሰ በኃላ / ከጆሮአቸው ጋር አገናኝተው ቢያስሩት የሚሻል መስሎኛል ፡፡ ምናልባትም ራሱን የቻለ ጌጥ ይፈጥርም ይሆናል ፡፡

ያልተሰራበት ኢንቨስትመንት

ሙርሲዎች ጨካኝ የሆነ ባህል ተከታይ መሆናቸውን ብዙዎች ይናገራሉ ፡፡ በተለይም በረጃጅም ዱላ የሚያደርጉት ድብድብ ወይም ዶንጋ ለወንድ ልጆች የጀግንነት ክብር መግለጫ ፣ የሚስት ማግኛ ብሎም የመከራ መቁጠሪያ ምዕራፍ ነው ፡፡ ለዚህ ባህላዊ ውድድር ጎረምሶች ተደራጅተው ይቀለባሉ ፡፡ ሙገሳና ጭፈራ ያጅባቸዋል ፡፡ በዚያው ልክ ተቀልበውም እስከወዲያኛው ሊያሸልቡ ይችላሉ ፡፡ የሀዘን ጥላም ዘወትር  ጎናቸው ነው ፡፡ ብዙ ግዜ ከዝናብ በኃላ ነው ውድድሩ የሚካሄደው ፡፡ የሙርሲ ወንድ ቢያንስ ከአንድ ወንድ ጋር ይህን ግጥሚያ ማከናወን አለበት ፡፡ አሸናፊው በሴቶች ተከቦ ወደፊት የሚፈልጋትን ሴት እንዲመርጥ ዕድል ያገኛል ፡፡

የአማራው ብሄረሰብ ‹ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ! › እንደሚለው ሁሉ ሙርሲዎችም በዶንጋ ለሚሞቱ ወጣቶች ጥብቅና አይቆሙም ፡፡ መቼም ነጭ የኖራ ስዕል ብቻ በለበሰ ባዶ ገላ በማይሰበር ዱላ ከመከትከት አንደኛውን የስፔን ቀውስ ሊግ ውስጥ ገብቶ በበሬ መወጋት ሳይሻል አይቀርም ፡፡

ሽማግሌዎች ዶንጋ ወጣቱ ህብረተሰብ መከራን እንዲችልና ጠላትም እንዳይፈራ ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዎጽኦ ይፈጥራል ባይ ናቸው ፡፡ ይህ ውድድር ህይወት እስከመቅጠፍ የሚያደርስ ከሆነ ላይቀር ሙርሲንም ሆነ ሀገሪቷን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የላቀ የኢንቨስትመንት ሀሳብ ማመንጨትይገባል ፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ አንድ ሃሰብ አለኝ ፡፡ ዶንጋ ልዩ በመሆኑ ብዙ የአለማችን ተመልካቾች አሉት ፡፡ ይህም ኢንቨስትመንቱን ለማስፋት አንደኛው ምቹ ሁኔታ ነው ፡፡ ከዚያም የዓለማችንን ምርጥ - ምርጥ ውግሪያዎች እየለቀሙ ማጥናት ፡፡ ዶንጋ ባህሉን ጠብቆ እንዴት ዓለማቀፍ ውድድር መሆን ይችላል የሚለውን ደግሞ ለጥቆ ማሰብ - መቀመር ፡፡

ለምሳሌ ያህል ብዙ ተመልካች ያለው የነጻ ትግል ስፖርት የሚከናወነው በፕሮሞተሮች ነው ፡፡ እነዚህ ፕሮሞተሮች ድርጊቱን በቴሌቪዥን ፣ በማስታወቂያ ፣ መጽሄትና ኢንተርኔት ያስተዋውቃሉ ፡፡ ታዋቂ ቡጢኞች በመዝናኛው ቻናል ብቅ እያሉ ቡራ ከረዩ እንዲሉ ያደርጋሉ ፡፡ እንግዲህ ይህ አሰራር በዚህ መልኩ ነው ቀስ በቀስ የአሜሪካ ታዋቂ ባህል እንዲሆን የተደረገው ፡፡

የታይላንድ ኪክ ቦክስንም ብንመለከት ከነጠላ መነሻነት ነው ዛሬ አድጎ ትልቅ ካፒታል መፍጠሪያ የሆነው ፡፡ የሀገሪቱ ወታደሮች ጠመንጃ በሌለበት ወቅት እንደ አጋር ተጠቅመውበታል ፡፡ ንጉሶች ለመዝናናት የጦር እስረኞች ደግሞ ለነጻነታቸው በዚህ ፍልሚያ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል ፡፡ ዛሬ ስፖርቱ ኤሽያን አልፎ አውሮፓ ደርሷል ፡፡ ተፋላሚ ተማሪዎች ‹‹ ንጹህ ፣ ጠንካራ ፣ ታማኝ ፣ አፍቃሪ እና በማንኛውም ግዜ ሌሎችን ለመርዳት የምተጋ እሆናለሁ ›› በማለት ቃል ይገባሉ

ካራቴንም ብንመለከት ከተፈጠረ ከ 1 ሺህ ዓመት በላይ አስቆጥሯል ፡፡ ሲጀመር በገዳም ተዘውትሮ የሚሰራ ጥበብ ቢሆንም ኃላ ላይ የቻይና ገበሬዎች ከታጠቁ ሽፍቶች ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ጋሻ አድርገውታል ፡፡ ቀስ በቀስ በመላው ዓለም በመዳረስ ለፊልምና ለተለያዩ ውድድሮች የማይነጥፍ ማዕድን ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ፡፡

በመሆኑም ዶንጋን እንደ ነጻ ትግል ፣ ኪክ ቦክስና ካራቴ የላቀ ደረጃ ለማድረስ የማይቻልበት ሁኔታ ስለማይኖር ጉዳዩን በጥሞና ማሰብ ይገባል ፡፡

ተንቀሳቃሹ ሸራ

በአንድ ከተማ ውስጥ 10 ሺህ ህዝብ ይኖራል እንበል ፡፡ ይህ ሁሉ ህዝብ ነጋዴ ፣ መሃንዲስ ወይም አንባቢ ሊሆን አይችልም ፡፡ የሙርሲ አስር ሺህ ህዝብ በሙሉ ግን ሰዓሊ ነው ፡፡ የራሱንና የሌሎች ገላ ላይ በነጭ ኖራ ቅርጻ ቅርጽ ያቀልማል ፡፡ አይነቱና ስልቱ ይለያይ እንጂ ሙርሲ የሰዓሊዎች ሀገር ነው ፡፡

የሀገራችን ሰዓሊዎች ስራዎቻቸውን ለተደራሲው የሚያቀርቡት ለተወሰነ ግዜ በጋለሪ ወይም በሚከራዩት ሆቴል ውስጥ ነው ፡፡ ለማየት እድል የሚያጋጥመውም በዛው መጠን በጣም ውስን ነው ፡፡ የሙርሲዎች የስዕል ሸራ ግን ሰውነታቸው በመሆኑ ጋለሪ ውስጥ የታጠረ አይደለም ፡፡ በየሜዳው ፣ በየተራራውና በየመንገዱ ይዘውት ይንቀሳቀሳሉ ፡፡ አላፊ አግዳሚውም ይመለከታቸዋል ፡፡ ሲፈልግ አብሮአቸው ፎቶ ይነሳል ፡፡ የሙርሲ ሰዓሊ ከከተማው የተማረ ሰዓሊ የሚቀርበት ጉዳይ ‹ ፈርምልኝ ? › የሚል ጥያቄ የሚያቀርብለት አለመኖሩ ነው ፡፡ ‹ ተንቀሳቃሽ ሸራ › መምሰሉን ግን ከተሜዎች በተሞክሮነት ሊያጤኗት የምትገባ ጉዳይ ናት ፡፡

ሙርሲዎች የሚጠቀሙት ስዕል አልፎ አልፎ ቀለል ያለ ቢሆንም አብዛኛው ግን ከአብስትራክት በላይ ይሆናል ፡፡ ለእነርሱ የቀለም አባቱ ነጭ ነው ፡፡ አንዳንዶች ነጭ ቀለም ከብትን ከማርባት ጋር ይያያዛል ይላሉ ፡፡ የስዕሎቹ መሰረት ክብ ፣ መስመር ፣ ነጥብ እና ግማሽ ክብ ናቸው ፡፡ የእነዚህ መገጣጠም ፣ መለያየት ፣ መደራረብ በአጠቃላይ መወሳሰብ ነው አይን በቀላሉ የማይፈታውን አብስትራክት የሚፈጥረው ፡፡

አንዳንዴ ሙሉ ሰውነታቸውን እንደ ሜዳ አህያ ይቀቡታል ፡፡ አንዳንዴ ሙሉ ፊታቸውን በወፈረው ነጭ ቀለም ይለስኑታል ፡፡ በየግዜው በእያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ላይ የሚታተሙ ስራዎች የተለያዩ መሆናቸውም ምናባዊ ፈጠራቸው ሰፊ መሆኑን ጠቋሚ ነው ፡፡ ጥቂት አብነቶችን ከጥቂት የሰውነት ክፍሎች ላይ መጎብኘት ብንጀምርስ ?

ፊት ፤

. ግንባርና ጉንጭን ብቻ መቀባት

. በጠቃጠቆ ቅርጽ መነጽር መስራት

. ግንባርና አፍንጫን በጠቃጠቆ ቅርጽ ቀብቶ ጉንጭንና አገጭን ሙሉ ነጭ መቀባት

. ሙሉ ፊትን በጠቃጠቆ ነጭ መቀባት

ሆድ ፤

.  የእጅ ምልክት

.  መጠኑ እየሰፋ የሚሄድ ቀለበት መስራት

.  በሶስት መስመር የሚታዩ ይይበልጣልና ያንሳል ምልክቶች

.  ሙሉ ነጭ ላይ በስሱ የሚታይ ዚግዛግ

.  ትናንሽ ብዙ ኮኮቦች

.  ይበልጣልና ያንሳል ፣ ክብና ዚግዛጎች ተደባልቀው

እንዲህ እንዲህ እያልን ብንጓዝ ገጻችንን ያሰፋዋል ፡፡ ዞሮ ዞሮ ቅርጽና ቀለሞቹ ትርጉም ባዘለ መልኩ እንደሚቀመጡ ይገመታል ፡፡ ምክንያቱም ስዕሎቹ ውስጥ የሂሳብ ፣ አስትሮኖሚ ፣ የእንስሳት፣ የተፈጥሮና የመሳሰሉ ብልጭታዎችን መመልከት ስለሚቻል ፡፡

በርግጥ ስዕሎቹን ለማወቅ ሰዓሊዎቹን ቀድሞ መረዳት ይጠቅማል ፡፡ አስተሳሰባቸው ፣ ፍልስፍናቸው ፣ የኑሮ ዘይቤያቸውና የእምነቶቻቸው ጸጋዎችን እየገለጹ ማንበብ የማንነታቸው መዳረሻ ላይ ያደርሳል ፡፡ ስዕል የውበታቸው መገለጫ ብቻ ሳይሆን የህልውናቸው ህገ ደንብ ወይም ህገ መንግስት ሆኖ ሊገኝ ይችላል ፡፡ ይህ ካልሆነ ታዲያ እንዴት የአንድ ሀገር ሙሉ ህዝብ ሰዓሊ ሆኖ ይገኛል ? ሁሉም ለራሱ ህገ መንግስት ታማኝና ተገዢ ቢሆን እንጂ ፡፡

ይህ ህገ መንግስት በኛ አባባል ማስፈጸሚያ ህጎችና ደንቦች ቢወጡለት ስዕላቸውን በኤግዚቢሽን መልክ በማሳየት መጠቀምም ዕውቀትን ማስተላለፍም ይችላሉ ፡፡ ተንቀሳቃሽም ሆነ ቋሚ ሙዚየም መፍጠርም እንደዛው ፡፡ ይህን ብዙ ሊነግረን የሚችል ተንቀሳቃሽ ሸራ ለፎቶ ማዳመቂያነት ከመጠቀም ባሻገር አቡጊዳውንም ለማጥናት መንቀሳቀስ ይጠበቃል ፡፡

ቅይጥ ዝመና

አንድ ፈረንጅ በብሎጉ ላይ ‹‹ The mursi people live in the stone age, hunt a little bit, the only modern part of their society is , getting money for photos which they spend for beer and other commodities of civilization ›› በማለት ጽፏል ፡፡

ከድንጋይ ዘመን ትውልድ ጋር የተመሳሰሉት ሙርሲዎች ብቸኛ የስልጣኔ መገለጫቸው ፎቶ ተነስተው በሚያገኙት ብር ቢራና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን መግዛታቸው ነው ፡፡ በርግጥ የዛሬ ሙርሲዎች ከላይ በጠቀስነው ዶንጋና ዱላ ብቻ የሚወከሉ አይደሉም ፡፡ ዛሬ ጥቂት የማይባሉት ከዱላ ይሻላል በማለት ይሁን ወይም በአማራጭነት ኤኬ ታጥቀዋል ፡፡

ሴት ወንዱ የታጠቀው ይህ መሳሪያ በሁለት ምክንያት እየተፈተሸ ነው ፡፡ አንደኛው እንደ ጠላት በፈረጇቸው ‹ ኛንጋቶም › በተባሉ ብሄረሰቦች ላይ ነው ፡፡ ሁለቱም ይፈላለጋሉ ፡፡ አንዱ የሌላውን ከብት ከመንዳት ወደ ኃላ አይልም ፡፡ በግጦሽና በመሬት ጉዳይ ይወዛገባሉ ፡፡ አንድ አካባቢ ሆነው እንጂ ኢትዮጽያና ኤርትራ ብሎ መፎተት ይቻል ነበር ፡፡

የሙርሲ ወንድ የዚህን ወይም የሌላ ጎሳ ወንድ ሲገድል እጅና ሰውነቱ ላይ በተለያዩ የሚያምሩ ስዕሎች ይበጣል ፡፡ ይህ ምልክትም እንደ ጀግንነት ማዕረግ ያገለግላል ፡፡ ገዳይን በባህል ወይም በህጋዊ መንገድ ከመገሰጽና ከመቅጣት ይልቅ ጠንካራ ተዋጊ መሆኑን ዕውቅና የመስጠት አሰራር ለነገ አንደኛው ስጋት መሆኑን አስምረንበት እንለፍ ፡፡

መሳሪያው እየተፈተሸበት የሚገኘው ሁለተኛው መንገድ ዝመና በፈጠረው የተሳሰተ መንገድ ወይም ዝመናን ባለመረዳት የመጣ ክስተት ነው ፡፡ ዛሬ ሙርሲዎች ጎረቤታቸው የሆኑትን ኮንሶዎች በመመልከት ‹ ቦርዴ › ብቻ አይደለም የሚጠጡት ፡፡ ጂንካ በመድረስ ባህላዊው አረቄ ላይ ደርሰዋል ፡፡ የሙርሲ መንደሮች ዛሬ በጀሪካን የተሞሉ አረቄዎችን በብዛት ‹ ኢምፖርት › ያስደርጋሉ ፡፡ አማርኛን የሚያቀላጥፍ የሙርሲ ወጣት ጉዳዩን በዝርዝር እንዳስረዳኝ ከሆነ ማህበረሰቡ በአረቄ ሀሴት ማድረግን እንጂ የኃላ የኃላ እያስከተለ ለሚገኘው የወንጀልና ጸጥታ ችግር ብዙም ቁብ አልሰጠውም ፡፡ በመሆኑም በአረቄ የደነዘዙ ወጣቶች በየጫካው በመሳሪያ በማስፈራራት መኪናዎችን ያስቆማሉ ፤ ይዘርፋሉ ፡፡ ለማምለጥ ሙከራ በሚያደርጉ ሾፌሮች ላይ ደግሞ ይተኩሳሉ ፡፡ የአንዳንድ መረን የለቀቁ ሙርሲዎች ባቄላ በርግጥም እየቆየች እንድትሄድ ከተፈቀደ የሀገር ውስጥና ውጭ ቱሪስቶችን ብሎም የመንግስትን ጥርስ የምታራግፍ ናት ፡፡

በገጠራማዎ ኢትዮጽያ የሚገኙ ህጻናት ፣ ወጣቶችና አዛውንቶች ቁልፍ ጥያቄ የሃይላንድ ላስቲክ ነው ፡፡ ይህ ሀሳብ ‹ የገጠር ልማት ስትራቴጂ › የሚለው መጽሀፍ ላይ ሰፍሮ ዘልየው ይሆን እንዴ ? ውሃ ማቆር … የወንዝ ውሃ … የጠብታ መስኖ … ውሃ ማጠንፈፍ … የሚሉ ሀሳቦችን የማስታውሰው ፡፡ በርግጥ ውሃና እርሻ ፤ ውሃና አርሶአደር ተመጋጋቢ መሆናቸው ተሰምሮበታል ፡፡

የውሃው ብቸኛ ማቆሪያ የሃይላንድ ወይም የአክዎ አዲስ ላስቲኮች መሆናቸውን ግን የሚሰብክ አይመስለኝም ፡፡ ተሻሽሎ ካልሆነ በስተቀር ፡፡ ‹ ጋሽዬ ፣ ወንድም የሃይላንድ ላስቲክ ስጠኝ ? › የሚለው የጥያቄ ግራፍ ግን ወደ ሰማይ እየተወረወረ ነው ፡፡ የኮንሶ ፣ የወላይታ ፣ ዶርዜ ህጻናት መኪና ሲያልፍ የሚያሳዩት ብሬክ ዳንስ ‹ ባዶ ሃይላንድ ስጠኝ › ለማለት ነው ፡፡ ቸር ከሆኑ ደግሞ ግማሽ ውሃ የያዘ ላስቲክ እንዲወረውሩ ፡፡ ዝም ብለው ከሄዱ ደህና ይግቡ ለማለት በትህትና እጃቸውን ያውለበልባሉ ፡፡ የሙርሲዎች ከሌላው የሚለየው አሰልቺም አስገዳጅም መሆኑ ነው ፡፡ የለም ! እያሏቸው ያለማቋረጥ ይለምናሉ ፡፡ መኪና አስቁመው ይጠይቃሉ ፡፡ ድንገት መኪናዎትን ለፎቶ ካቆሙ ሁሉንም ክፍሎች በፍጥነት መቆለፍ ይኖርቦታል ፡፡ አለበለዚያ ባዶ ሃይላንድ አይደለም ውሃ የያዙ ላስቲኮችን መንጭቀው ይወስዳሉ ፡፡ ወርደው ለማስፈራራት ሲሞክሩ ውሃውን መጠጣት ጀምረዋል ፡፡ ሌላ የማያውቁትን ዕቃ ጩልፍ አድርገው ይሮጣሉ ፡፡ ይህን መዝረፍ እያሉ ሊጠሩ ቢችሉም ለእነሱ አንደኛው ‹ ጥሩ ጸጋ › ሊሆን ይችላል ፡፡ ምክንያቱም ከብት የሌላቸው ትዳር ፈላጊ ወጣቶች የጥሎሽ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ከኛንጋቶም ወይም ከሌላ ብሄረሰቦች ዘንድ ዘርፈው በማምጣት ነው ፡፡ ይህም ጀግና እንጂ ሌባ አያሰኝምና ፡፡

ሙርሲዎች ባህላዊ ማንነታቸውን ጠብቀው ለመጓዝ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም እየሞከሩ የሚገኙት የዝመና ዘይቤዎች ወዳላስፈላጊ መንገዶች እየመሯቸው ነው ፡፡ ጠመንጃ ለምን እንደሚያዝና እንደምን መተዳደር እንደሚገባው የአፋርን ተሞክሮ መቅሰም ይገባል ፡፡ የሰው መግደልና መዝረፍ ትርጉም በአካባቢው አውድ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ በሆነ ማዕቀፍ ውስጥ እንዴት

እንደሚገልጽ ሳይውል ሳያድር እንዲገነዘቡ ማድረግ ግድ ይላል ፡፡ የስነምግባርና እንግዳ ተቀባይነት ደረጃቸውም ከፍ እንዲል መሰራት ይኖርበታል ፡፡ በቱሪዝም ልማት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እየፈለግን በፍም ለሚደረጉ ጨዋታዎች ዕውቅና መስጠት አንችልም ፡፡ ፍሙን ችላ ካልነው የቱሪስትን ዶላር ብቻ አይደለም የሚያቃጥለው… ፍሙን ችላ ካልነው የሚያስጎመጀውን ደን ብቻ አይደለም የሚያከስለው … ፍሙን ችላ ካልነው የዱር እንስሳት ሀብቱን ብቻ አይደለም የሚያወድመውና ለስደት የሚዳርገው … ፍሙ ሰብዓዊ ሀብቱንም ይቀረጥፋል ፤ እረ ፖለቲካውንም ጭምር ፡፡

ይህ ጽሁፍ በቁም ነገር መጽሄት የጥር - የካቲት ዕትም ላይ የወጣ ነው

 

 

 

 

Views: 917

Tags: ethiopian, mursi, travel, tribe

Comment

You need to be a member of Sodere Ethiopian News and Entertainment to add comments!

Join Sodere Ethiopian News and Entertainment

SodereTube Ethiopian News

The train in com'n - The latest Addis light rail video

The train in com'n - The latest Addis light rail video

{AFERSATA} Innocent man accused of murder stand on trial - Story on Sheger FM

{AFERSATA} Innocent man accused of murder stand on trial - Story on Sheger FM

The insider News Part 2.

The insider News Part 2.

Things every young men and women should do before turning 40

Things every young men and women should do before turning 40

BBC: Is journalism a crime in Ethiopia? Journalists in exile and government rep respond

BBC: Is journalism a crime in Ethiopia? Journalists in exile and government rep respond

SodereTube Comedy

Betoch comedy Part 87

Betoch comedy Part 87

Nuroachen Comedy Part 16

Nuroachen Comedy Part 16

Ethiopia Nuroachen Comedy Part 15 only on Sodere Cinema

Ethiopia Nuroachen Comedy Part 15 only on Sodere Cinema

Nuroachen Comedy Part 14 only on SodereTube

Nuroachen Comedy Part 14 only on SodereTube

Ethiopian Comedy - Yarefede Arada - Sodere Cinema and Selam Production

Ethiopian Comedy - Yarefede Arada - Sodere Cinema and Selam Production

Ethiopian Drama

Mogachoch Drama Part 17

Mogachoch Drama Part 17

Wazema Drama Part 3

Wazema Drama Part 3

Dana Drama Part 75

Dana Drama Part 75

Mogachoch Part 15

Mogachoch Part 15

Dana Drama Part 73

Dana Drama Part 73

Events

EthiopianTube Music

Balageru Idol Helen Gedey Sings Eden G.Selassie's Sewenwano Balageru Idol 4th Audition

Balageru Idol Helen Gedey Sings Eden G.Selassie's Sewenwano Balageru Idol 4th Audition

Balageru Idol Zemach Dance Crew Best Performance Balageru Idol 3rd Round

Balageru Idol Zemach Dance Crew Best Performance Balageru Idol 3rd Round

Balageru Idol Girma Assefa Performance on balageru Idol 4th Round

Balageru Idol Girma Assefa Performance on balageru Idol 4th Round

Mesekerem Alemayehu - Balageru Idol 4th round

Mesekerem Alemayehu - Balageru Idol 4th round

Ethiopian Videos

Incredible Story Telling - Letter to my cloth "Debeloye" by Fikadu Teklemariam

Incredible Story Telling - Letter to my cloth "Debeloye" by Fikadu Teklemariam

Marriage that was about to end saved - Women who left her family and went to arab country

Marriage that was about to end saved - Women who left her family and went to arab country

My sweet Memory when I Was A Kid - 'Kiss Buddy' "Yekenfer Wedaj"

My sweet Memory when I Was A Kid - 'Kiss Buddy' "Yekenfer Wedaj"

Things Wives Do That Drive Husbands Away

Things Wives Do That Drive Husbands Away

Jossy in Z House Show - Ethiopian Christmas Special 2015 / 2007 E.C

Jossy in Z House Show - Ethiopian Christmas Special 2015 / 2007 E.C

Ethiopian news and video portal. Sign in create profile, share videos, upload picture, invite your friends and have fun.

SodereTube Sport

Land to be used to build 60 thousand seat Adey Abeba stadium almost ready

Land to be used to build 60 thousand seat Adey Abeba stadium almost ready

Dire Dawa to construct 60 thousand seat stadium

Dire Dawa to construct 60 thousand seat stadium

Arsenal's Ghedion Zelalem commented on his first Champions League game

Arsenal's Ghedion Zelalem commented on his first Champions League game

Very Funny Comedy - Goalkeeper's face destroyed after he saves five goals with his face

Very Funny Comedy - Goalkeeper's face destroyed after he saves five goals with his face

Ethiopia vs Malawi Live Commentary

Ethiopia vs Malawi Live Commentary

© 2015   Created by Sodere.

Badges  |  Report an Issue  |  Terms of Service